Ministry of Education
ትምህርት የሰው ልጅ በኑሮ ትግሉ ያከማቻቸውን ግኝቶችንና ተሞክሮዎችን ማስተላለፊያና አዲስ ግኝቶችን ማፍለቂያ ሂደት ነው፡፡ ትምህርት ግለሰቦችን በእውቀት፣ በግንዛንቤ፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣በሥነ-ውበትና በእሴት እንዲሁም በችሎታና በክህሎት በማነጽ ለራሳቸውና ለኀብረተሰብ ሁለንተናዊ እድገት ፍሬያማ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ የትምህርት ሂደት በግለሰብና በኀብረተሰብ ተስተጋብሮት ለአጠቃላይ ኀብረተሰብ ህልውናና እድገት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ስለሆነም በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡
የትምህርት አንዱ ባሕርይ መሠረታዊ እውቀት በማስጨበጥ፣ በግለሰብም ሆነ በኀብረተሰብ የችግር ፈቺነት አቅምን፣ ችሎታን ባህልን ማጎልበት ነው፡፡ በመሆኑም ትምህርት ጎጂ ባህሎችን በመለየትና በማስወገድ፣ ጠቃሚና አዲስ ባህሎችን በመቅሰምና በማዳበር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በኀብረተሰቡ በማስረጽ፣ የሰው ልጅ አካባቢውን እንዳስፈላጊነቱ አሻሽሎና ለውጦ በሚገባ ተንከባክቦና አልምቶ ለሁለንተናዊ እድገቱ እንዲያውለው ይረዳዋል፡፡ ከዚህ ጋር ነፃነት፣ መብትና ግዴታ ማኀበራዊ ለሰብአዊ መብቶች መከበርና እኩልነትና መግባባት እንዲኖር በአጠቃላዩም ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መስፈን ትምህርት የበኩሉን ሚና ማሟላት ይኖርበታል፡፡
ትምህርት ብቻውን ተነጥሎ የሚከናወን ሳይሆን ከምርምር ከሙያዊ ተግባርና ከልማት ጋር ተስተጋብሮ ለኀብረተሰቡ ሁለንተናዊ እድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡
የሀገራችን ትምህርት ሁኔታ በዓላማ በይዘት በአቀራረብ በሥርጭት በግባትና በሂደት እንዲሁም በውጤት ሲታይ ተማሪዎች ተገቢውን ትምህርት ቀስመው የችግር ፈቺነት ባሕርይንና ችሎታን እንዲያጎለብት አስችሎአቸዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል ተገቢውን ባህል በማዳበር ሳይንስና ቴክኖሎጂን በፀብረተሰቡ አስርጾ አካባቢያቸውን ለመንከባከብ ለማልማትና ማኀበር-ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎአቸውን ለማጠናከር እንዲያስችላቸው ያደረገው አስተዋጽኦ ጎልቶ አልታየም፡፡
በሥርጭቱም ረገድ ዕድሜአቸው ለትምህርት ከደረሱት መካከል በተለይ በአንደኛ ደረጃ የሚሳተፉት ከ22 በመቶ በታች ሲሆኑ፣ ከነዚህም ከዝቅተኛ ክፍል አቋርጠው ወደ ማይምነት የሚመለሱት በርካታ ናቸው፡፡ በክልሉች መካከል ያለው ተሳትፎ ሲታይም ሥርጭቱ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ በአጠቃላጥ ሰፊ የማይምነት ችግር መኖሩ በግልጽ ይታያል፡፡ የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ችግሮችም እንደዚሁ የጎሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ በእነዚህ ደረጃዎች የትምህርት ተገቢነትና ጥራት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል በከፍተኛ ትምህርት በሳል ችግር ፈቺ ምሁራንን በማፍራትም ሆነ ለሕዝብ ጥቅምና ለሀገር እድገት የሚጠበቀውን ያክል የጥናትም ሆነ የምርምር ውጤት ጎልቶ አልታየም፡፡